ዜና

ኢንስቲትዩቱ የ2017 አዲስ አመት በማስመልከት የማዕድ ማጋራት ፕሮግራም አካሄደ።

የእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት አዲስ አመትን አስመልክቶ የበዓል ማዕድ ማጋራት አካሂዷል።  ጳጉሜ 5 ቀን 2016 ዓ.ም ኢንስቲትዩቱ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የወረዳ 7 ቀጠና 4 እና 5 ለሚኖሩ 15 አቅመ ደካማ እማወራ እና አባወራ የማዕድ ማጋራት ፕሮግራም አካሂዷል።

በእለቱ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢንስቲትዩቱ ም/ዋ/ዳይሬክተር ዶ/ር ዳኛቸው በየነ ተቋማችን ከዝርያ ማሻሻል ምርትና ምርታማነት እንዲሁም የሌማት ትሩፋት ስራዎች ከመስራት ጎን ለጎን ሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮችን እንደ ሀገር እየተወጣ የሚገኝ ተቋም መሆኑን ገልፀው የማዕድ ማጋራት ተግባራችን እንደ እርዳታ ሳይሆን እንደ አንድ ጎረቤት እንኳን አደረሳችሁ ለመባባል እና መልካም ምኞታችንን ለመግለፅ በማሰብ በመሆኑ መጪው ዘመን የጋራና የአብሮነት ስሜት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በማሰብ ነው ብለዋል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ትብለፅ ገ/ዮሀንስ ተቋማችን በርካታ ማህበራዊ ጉዳዮችን እየተወጣ መሆኑን ገልፀው  የዛሬውን ማዕድ ማጋራት ተግባርም የዚሁ አካል መሆኑን ገልፀው ይህ ተግባር ቀጣይነት ያለውና ሌሎች ያልተረዱ አካባቢዎችንም በማየት እየተጠናከረና እየሰፋ የሚሄድ በጎ ተግባር እንደሚሆን ገልፀዋል።

የወረዳ 7 ዋና ስራ አስፈፃሚ ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ መልካሙ ወንደሰን ኢንስቲትዩቱ ከማዕድ ማጋራት ውጪ ሌሎች በርካታ ስራዎችን ከትራንስፖርት ጀምሮ በማገዝና በመስራት ከፍተኛ እገዛዎችን እያደረገ ያለ ተቋም መሆኑን ተናግረው ምስጋናቸውንም ገልፀዋል።

በመጨረሻም በዕለቱ ለተገኙ እማወራና አባወራዎች ዶሮ, እንቁላል, ዱቄት, ዘይትና ሽንኩርት ተበርክቶላቸዋል።

ዘጋቢ ወ/ሮ ዞማነሽ ውድነህ

ካሜራ ወ/ሮ  ቤተልሄም ማንደፍሮ